የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በክልሎች ማዘጋጃ ቤት ስር ለሚገኙ ለእንስሳት ህክምና አንዲሁም ቄራን ማእከል በማድረግ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱ ተገልጿል፡፡
መጋቢት 12፤ቀን 2015 ዓ.ም
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ከተማ መሰረተ ልማት ሚኒስትር ከእንስሳት ወደ ሰዉ የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል በመሆኑም በሁሉም ክልሎች ማዘጋጃ ቤት ስር በሚገኙ ቄራዎች ዉስጥ ለሚሰሩ የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ከእርድ እንስሳት ጋር ተዛማጅ የስራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አካላት ከአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ስልጠናዉ በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት መከናወኑ ድርጅቱ በዘርፉ ከ60 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረና በርካታ ልምዶችን ያካበተ ቄራ በመሆኑ እና በአደረጃጀቱና በመዋቅሩ በአገሪቱ ዉስጥ ከሚገኙ ቄራዎች የተሻለ ልምድ ያለዉ አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ ያለዉን ልምድ ለማካፈል እድል የሚፈጥር ከመሆኑ አንፃር ስልጠናዉን ለማከናወን ተመራጭ እንዳደረገዉ የድርጅቱ የሰዉ ሀይል ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ደመቀ ኪሮስ ገልፀዋል፡፡
የስልጠናዉ ዋና አላማ በእርድ አማካኝነት ከእንስሳት ወደ ሰዉ የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል በዘርፉ በቂ ባለሙያዎችን በማሰልጠንና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንዲወስዱ በማድረግ ዘርፉ የሚፈልገዉን ስታንዳርድ በጠበቀ መልኩ ባለሙያዎችን በማብቃት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንዲያገኙ ማስቻልን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ፡፡
በስልጠናዉ ላይ ከኦሮሚያ፤አማራ፤ደቡብ፤ጋምቤላ እንዲሁም ሀረሪ እና አዲስ አበባ የተወጣጡ 48 ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ለሁለት ሳምንታት በእንስሳት ህክምናና በእንስሳት እርድ ስራ ላይ በቂ እዉቀትና ልምድ ባላቸዉ አሰልጣኞች በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና ተሰጥቷል እንዲሁም ምዘናዉ ከአዲስ አበባ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በመጡ መዛኞች የተከናወነ ሲሆን 45 የሚሆኑት ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ምዘናዉን በማለፍ የምስክር ወረቀት ወስደዋል ሲሉ ዳይሬክተሩ ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ድርጅቱ የስትራቴጄክ እቅዱ አንዱ አካል የሆነዉ ደረጃዉን የጠበቀ የስልጠና ማእከል በማቋቋም የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም ስልጠና ከሚሰጡ አካላት ጋር በጋራ መስራት ሲሆን የተከናወነዉም ስልጠና ለተያዘዉ እቅድ ትልቅ ልምድ የተገኘበት እንደሆነ የተቋሙ የሰዉ ሀይል ዳይሬክተር አያይዘዉ ገልጸዋል፡፡